Thursday, November 7, 2024

የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ፦ የማቴዎስ ወንጌል 4

1 ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥

2 አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ።

3 ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።

4 እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው።

5 ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ፦

6 መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።

7 ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው።

8 ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፦

9 ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።

10 ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።

11 ያን ጊዜ ዲያብሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።

12 ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ።

13 ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ።

14-16 በነቢዩም በኢሳይያስ፦ የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።

17 ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።

18 በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና።

19 እርሱም፦ በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው።

20 ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።

21 ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም።

22 እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።

23 ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።

24 ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም።

25 ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።

No comments:

Post a Comment